Message From Director General

የዋና ዳይሬክተሩ መልእክት

የግብርናው ኢኮኖሚ ከ95 በመቶ በላይ የሀገር ወስጥ የምግብ አቅርራቢ፣ ከ80 ሚሊዮን በላይ የቤተሰብ አባላትን የሚደግፍ፣ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ አምራች አባዎራዎች መተዳደሪያ፣ ከ80 በመቶ በላይ የውጪ ምንዛሪ ማስገኛ፣ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ቁልፍ ዘርፍ፣ ለምግብ ኢንዱስትሪ፣ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ለኬሚካል፣ ለፋርማቲካል፣ ለዲተርጀንት፣ ለኮንስትራክሽን፣ ወዘተ ኢንዱስትሪዎች ከ60 በመቶ በላይ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ማቅረብ የሚችል የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከማንኛውም የሀገራችን የኢኮኖሚ ዘርፎች በተሻለ ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሻ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም የሀገራችን ግብርና ምርት አመራረት የዝናብ ጥገኛ ከመሆኑም በላይ ኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ፣ የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦትና አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን፣ የአርሶ አደሮች አቅም ውስንነት ችግሮች ገና አልተላቀቀም፡፡

የግብርና ልማት (ምርትና ምርታማት ዕድገት) በሚገባ ሊሳካ የሚችለውም የልማቱ ተቀዳሚ ተቋዳሽ መሆን ያለበት አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ በላይ በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በበቂ መጠንና በሚፈለገው ጥራት ማቅረብ ሲችል ነው፡፡ አምራች አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ በላይ በማምረት ለገበያ ለማቅረብ የሚበረታታው ደግሞ ላቀረበው ምርት ተገቢውን ዋጋ ማግኘትና አመራረቱን ወደ ዘመናዊ ገበያ ተኮር ወይም የንግድ ወይም ገበያ ተኮር ግብርና መሸጋገር ሲችል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ትርፍ ምርት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ይቅርና የራሱን ፍጆታ ለማምረት የሚበረታታ አይሆንም፡፡ አምራች አርሶ አደሩ ግብርናውን ወደ ገበያ ተኮር ወይም የንግድ ግብርና እንዲሸጋገር ለሚያመርታቸው ምርቶች ተገቢውን ዋጋ ማግኘት ሲችል ነው፡፡

የግብርናው ኢኮኖሚ ዘርፍ ሁለት ፈርጆች (አቅርቦትና ፍላጎትን) የሚያገናኝ ድልድይ ደግሞ የግብርና ምርት ገበያ ወይም የግብይት ሥርዓት ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ደግሞ በግብይት መሠረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የገበያ መረጃ በበቂ መጠን ተደራሽ አለመሆን እና ወጪ የሚጨምሩ ረጃጅም የግብይት ሰንሠለቶች የሚታዩበት ነው፡፡ ገበያ ተኮር የሆነ የግብርና ልማት አለመስፋፋት፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን፣ የግብይት ወጪ መናር እና የመሳሰሉት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ የግብርና ምርቶች ግብይት በልማዳዊ የግብይት ሥርዓት የሚካሄድ በመሆኑ ለአምራቹ ተገቢ ዋጋ ለማስገኘት አለመቻሉና አምራቹን የሚያበረታታ አለመሆኑ፣ የግብይት ሥርዓቱም በከፍተኛ የግብይት ወጪ የሚከናወን ተገቢ የገበያ ውድድር የሌለበትና የምርት ጥራትን ለማሳደግ ማበረታቻ የማይሰጥ መሆኑ በዋናነት የሚጠቀስ ነው::

የግብርና ምርት የግብይት ሥርዓት ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግስት ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል ልማዳዊ የግብርና ግብይት ሥርዓት ወደ ዘመናዊ የግብርና ምርት ግብይት ሥርዓት ለማሸጋገር የግብርና ምርቶች ግብይት ስትራቴጂ ተቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ የግብርና ምርቶች ግብይትን ለማሻሻልና በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በአራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው የምርት ጥራት የሚሻሻልበትንና ለምርቶች ደረጃ የሚወጣበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ ሁለተኛው የገበያ መረጃ ለአርሶ አደሩ የሚሠራጭበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ሦስተኛው በተበጣጠሰ አነስተኛ ማሣ ምርት የሚያመርቱ አርሶአደሮችን በማሰባሰብ በኅብረት ሥራ ማኅበራት/ዩኒየኖች በኩል የገበያ ተሳትፏቸውን ማሳደግ ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ በግብይቱ ላይ የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ነው፡፡

በቀጣይም በሁሉም ምርቶች ከመሬት አያያዝና ዝግጅት ጀምሮ ምርቱ ወደ ማከማቻ እስኪገባ ወይም ለግብይት አስኪቀርብ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በመደገፍ በአነስተኛ ወጪ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ፣ የምርት ጥራትን የሚሻሻሉ እና አቅርቦት መጠንን የሚያሳድጉ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ለምርቶቹ ተጨማሪ የገበያና ግብይት አመራጭ ችግር በመለየት እንዲሁም የዋጋ አለመረጋጋትን በመቆጣጠር የማሻሻል ስራው ይቀጥላል፡፡ በየድህረ-ምርት አሰባሰብ፣ አያያዝና ጥረት አጠባበቅ በአዳዲስ በቴክኖሎጂዎች የተደገፈ ጥረት ማድረግ እንዲሁም በዝናብ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀረፍ ጥረቶች መቀጠል አለባቸው፡፡ በዚህ አርሶ አደሩ ምርቱን ለማምረት የሚያወጧቸው ወጪዎች በመቀነስ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እና ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያለንን ተወዳዳሪነት ለማጐልበት ይቻላል ተብሎ ይታመናል፡፡

ይህን መሰረት በማድረግ በአገራችን ከፍተኛ የሆነ ካፒታል በማፍሰስ መንግስት ዘመናዊ የግብይት ስርዓትን በመዘርጋት ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ከሥርዓቱ መፈጠር ጋር ተይይዞ አጠቃላይ የግብይቱን ስራዎች የሚከውን እንዲሁም አሰራሩን እና ስርዓቱ የሚቆጣጠሩ ተቋማት በ2000 ዓ.ም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሂደት ተግባራት የሚመራ ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 550/1999 ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን የግብይት ሂደቱን እና አጠቃላይ አሰራሩን የሚቆጣጠር ተቋም በመሆን በአዋጅ ቁጥር 551/1999 ተቋቁሞ በ2000 ዓ.ም ወደ ተግባር ተሸጋግሯል፡፡ በአገራችን ይህንን ተከትሎ በርካታ ምርቶች ወደ ዘመናዊ የምርት ግብይት አሰራር የገቡ ሲሆን ለግብይቱ ተዋንያን አገልግሎቱም ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ 23 የአገራችን አካባቢዎች የምርት መረከቢያ መጋዘኖች ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ባለሥልጣኑም እነዚህን የግብይት መረከቢያ ማዕከላት በቅርበት ለመከታተል እና አሰራራቸውን ለመቆጣጠር በአራት የክልል ከተሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በመክፈት በአዋጅ የተሰጡትን ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በሀገራችን ውጤታማ የሆነ ዘመናዊ የመገበያያ ስርዓት ለመገንባት የዘመናዊ ምርት ግብይት መርሆዎች በህብረተሰቡ እንዲሰርጽ በማድረግ የገበያ ስርዓቱን የሚያናጉ እንቅስቃሴዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን የማረጋግጥ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

በቀጣይም ሁሉም የባለሥልጣኑ ሰራተኞች እና የምርት ገበያው ሰራተኞች እና የግብይቱ ተዋንያን  ሥራ ውጤታማ ለመሆን በሚያስችላቸው መንገድ በመጓዝ በዘርፉ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት ካለፉት ጊዜያት በበለጠ ትጋትና በጥንቃቄ መንቀሳቀስ ይገባናል፡፡

አገራዊ ለውጡን በጋለ ስሜት በማስቀጠል በንግድ ዘርፉን የተቀመጡትን  የለውጥና የሪፎርም ዕቅዶች በሚገባ ለመተግበር ከድህንነት ለመውጣት እና ወደ ብልጽግና ለምናደርገው ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ ሁላችንን የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማበርከት ይበቅብናል፡፡