ECX Employees Code of Ethics Directive No 561- 2013 (2)

       የምርት ገበያ ሠራተኞች የሥነ-ምግባር መመርያ ቁጥር 561/2013

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለልጣን ውጤታማ የሆነ የዘመናዊ ምርት ግብይት ርዓት መገንባቱን የማረጋገጥ፣ የምርት ገበያው አስተማማኝ፣ ግልጽ እና የተረጋጋ አራር እንዲኖረው የመቆጣጠር እንዲሁም በገበያው የሚሳተፉትንም ሆነ በአጠቃላይ የህብረተሰቡን ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣

ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንዲቻል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ራተኞች እና የራ ኃላፊዎች መልካም ነ-ምግባር ተላብሰው እና ሕግን አክብረው ራቸውን እንዲያከናውኑ ለማድረግ የሚያስችል የሥነ-ምግባር መከታተያና መቆጣጠሪያ መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

እነዚህን ዓላማዎች ለማስፈጸም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለልጣን በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 551/1999 /እንደተሻሻለው/ አንቀጽ 6(11) እና አንቀጽ 34(2) በተሰጠው ልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

 አንቀጽ 1አጭር ርዕስ

ይህ መመርያ “የምርት ገበያ ሠራተኞች የነ-ምግባር መመርያ ቁጥር 561/2013” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

አንቀጽ 2ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመርያ ውስጥ፤

2.1  ባለሥልጣን” ማለት በአዋጅ ቁጥር 551/1999 /እንደተሻሻለው/ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለልጣን ነው፡፡

2.2 “የምርት ገበያ” ማለት በአዋጅ ቁጥር 550/1999 /እንደተሻሻለው/ የተቋቋመው

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው፡፡

2.3 ራተ” ማለት በምርት ገበያው ውስጥ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት/በኮንትራት ተቀጥሮ የሚሠራማንኛውም ሰው ነው፡፡

2.4 “የሥራ ኃላፊ” ማለት በምርት ገበያው በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት/በኮንትራት ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ የሥራ ዘርፍ ዳይሬክተር፣ ኦፊሰር፣ የጽ/ቤት ኃላፊ፣ የመጋዘን ኃላፊ፣ የአገልግሎት ኃላፊ፣ የቡድን አስተባባሪ፣ ሱፐርቫይዘር፣ ወይም በሌላ ስያሜ በሚጠራ ተመሳሳይ የኃላፊነት ደረጃ የሚሠራ ሰው ማለት ሲሆን የምርት ገበያውን ዋና ራ አስፈጻሚ እና ምክትሎቹን እንዲሁም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን አይጨምርም፡

2.5 “የጥቅም ግጭት” ማለት ማንኛውም ሠራተኛ ወይም ሥራ ኃላፊ ቤተሰብ ወይም የቅርብ ዘመድ የገንዘብ ወይም ሌላ ዓይነት ጥቅም ከሠራተኛው ወይም ከሥራ ኃላፊው መደበኛ ሥራ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጋጭ ወይም ግጭት ሊፈጥር የሚችል ሲሆን ነው፡፡

2.6 “ቤተሰብ” ማለት የሠራተኛው ወይም“ ሥራ ኃላፊው ባል/ሚስት፣ ወይም በስሩ የሚተዳደር ዕድሜው 18 ዓመት ያልሞላው ልጅ ማለት ሲሆን ጋብቻ ሳይፈጽም እንደባልና ሚስት አብሮ የሚኖርን ሰውና የጉዲፈቻ ልጅን ይጨምራል፡፡

2.7 “የቅርብ ዘመድ” ማለት የሠራተኛው ወይም“ ሥራ ኃላፊው ወይም የባል/ሚስት ወላጅ፣ ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ልጅ፣ እህት፣ ወንድም፣ እና ሌሎች እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያላቸውን ሰዎች ያጠቃልላል፡፡

2.8 “ስጦታ” ማለት ሠራተኛው ወይም የሥራ ኃላፊው ለደንበኛ ለሰጠው አገልግሎት ወይም የምርት ገበያው ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ለራሱ ወይም ለቤተሰብ አባል ወይም ለቅርብ ዘመድ የተሰጠ ገንዘብ ወይም የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው ማንኛውም ነገር ነው፡፡

2.9 “መስተንግዶ” ማለት ሠራተኛው ወይም የሥራ ኃላፊው ለደንበኛ ለሰጠው አገልግሎት ወይም የምርት ገበያው ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ለራሱ ወይም ለቤተሰብ አባል ወይም ለቅርብ ዘመዱ የተደረገለት ነፃ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የመጓጓዣ፣ የመኝታና የመዝናኛ አገልግሎት ነው፡፡

2.10 “ጥቅምን ማሳወቅ” ማለት በሠራተኛው ወይም በሥራ ኃላፊው መደበኛ ሥራ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል ወይም ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ሠራተኛውን ወይም “ሥራ ኃላፊውን ወይም የቤተሰቡን የፋይናንስ ወይም ሌላ ዓይነት ጥቅም ወይም ሀብት ለምርት ገበያው እና ለባለሥልጣኑ በፅሁፍ ማሳወቅ ማለት ነው፡፡

2.11 “ሚስጢር መጠበቅ” ማለት ሠራተኛው ወይም የሥራ ኃላፊው በሥራ አጋጣሚ ያገኘውን

እንዳይገለፅ ክልከላ የተደረገበትን መረጃ ከሥራ ዓላማ ውጪ ለማይመለከተው አካል

አለመግለፅ ማለት ነው፡፡

2.12 “ማጭበርበር” ማለት ሠራተኛው ወይም የሥራ ኃላፊው ማንኛውም ምክንያታዊ/ሚዛናዊ ሰው ወይም የምርት ገበያ ሠራተኛ በጠቅላላ እውቀት ወይም በሥራ ልምድ ትክክል አለመሆኑን የሚያውቀውን ወይም ሊያውቀው የሚገባውን አንድ ነገር ሌላውን ሰው ለመጉዳት ወይም ለራስ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ትክክል አስመስሎ የማቅረብ ድርጊት ነው፡፡

2.13 “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡

2.14 በዚህ መመርያ በወንድ ታ የተገለፀው የሴትንም ታ፣ እንዲሁም በነጠላ ቁጥር የተገለፀው ብዙ ቁጥርን፣ በብዙ ቁጥር የተገለፀው ነጠላ ቁጥርን ይጨምራል፡፡

 አንቀጽ 3ተፈጻሚነት ወሰን

ይህ መመርያ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

ንቀጽ 4የመመርያው ዓላማ

4.1 የዚህ መመርያ አጠቃላይ ዓላማ የምርት ገበያው ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ሥራቸውን በሚሠሩበት ወቅት ሊከተሏቸው የሚገቡ የሥነ-ምግባር መርሆችን በሕግ በግልፅ በማስቀመጥ የእለት ከእለት ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዲችሉ ለመርዳትና የሥነ-ምግባር ጥሰቶች ሲፈጸሙ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት የዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ፍትሐዊ፣ ግልፅ እና ተአማኒነት ያለው እንዲሁም የግብይት ተሳታፊዎችን እና በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ጥቅም ያስጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

4.2 ከዚህ በላይ የተመለከተው አጠቃላይ ዓላማ እንደተጠበቀ ሆኖ መመሪያው የሚከተሉት ዝርዝር ዓላማዎች ይኖሩታል፤

ሀ. የግልፅነት እና የተጠያቂነት የሥራ ባህልን በማዳበር አድልዎ የሌለበት የአገልግሎት አሰጣጥ ማስፈን፣

ለ. የሕዝብ አገልጋይነት ባህል በማዳበር ለኅብረተሰቡ ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት መስጠት፣

ሐ. ሙስናን እና ብልሹ አሠራሮችን የሚዋጋ በሥነ-ምግባር የታነፀ ሠራተኛ እና የሥራ ኃላፊ

በማፍራት በምርት ገበያው መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣

መ. የሥነ-ምግባር ግድፈቶች እንዳይፈጸሙ መከላከል፣ ተፈጽመው ሲገኙ የእርምት እርምጃ

ለመውሰድ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፡፡

ክፍል ሁለ

የምርት ገበያው ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ሊተገብሯቸው የሚገቡ የነ-ምግባር ደንቦችና መርሆች

 አንቀጽ 5ሀቀኝነት

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

5.1 ከሙስና፣ ከአታላይነትና ከአጭበርባሪነት በፀዳ ሁኔታ በሀቀኝነት መሆን አለበት፡፡

5.2 ፖሊሲን በሚመለከት የሚያማክር ከሆነ ትክክለኛና ያልተዛባ ምክር መስጠት አለበት፡፡

5.3 ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት በደንበኞች ወይም በኅዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት ከሚያደርስ ተግባር መቆጠብ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 6የተሟላ ስብዕና

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

6.1 ህብረተሰቡ በምርት ግብይት ሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዲኖረው ለማድረግ በመልካም ስነ ምግባር፣ በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት፣ ጥንቃቄ እና ትጋት መስራት አለበት፡፡

 • ማንኛውንም የሕግ ጥሰት የምርመራ ወይም የክትትል ሥራ በሚያከናውንበት ጊዜ የሚመረምረውን ጉዳይ በተጨባጭ ማስረጃ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
 • ከሚያከናውነው ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን በየጊዜው የሚወጡትን የሀገሪቱን ሕጎች፣ የባለሥልጣኑን መመሪያዎች፣ የምርት ገበያውን የውስጥ ደንብ እና ሥራውን የሚያከናውንበትን የአሰራር ማንዋል እየተከታተለ አውቆ መገኘት አለበት፡፡
 • ከሥራው ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚያድገውን የምርት ግብይት ሕግ አስተሳሰብ እና የአሠራር መሻሻል በመከተል ዘወትር ዕውቀቱን ማዳበር አለበት፡፡
 • በምርት ገበያው እና በባለሥልጣኑ በሚዘጋጁ የአቅም ግንባታ ኘሮግራሞች ላይ በመሳተፍ የአሰራር ችሎታውን ያለማቋረጥ ማሻሻል አለበት፡፡

አንቀፅ 7አድሎ አለመፈጸም

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን አድሎ በሌለበት ሁኔታ ተገቢና ፍትሐዊ በሆነ አኳኋን ውሳኔ የመስጠት እና ሁሉንም ደንበኞች ያለ አድሎ እና በእኩልነት የማገልገል ግዴታ አለበት፡፡ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር/በብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በአካልጉዳት፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ምክንያት የተለየ እንክብካቤ ወይም ልዩነት ሳያደርግ የቀረበለትን ጉዳይ ፍሬ ነገር እና ሕግን መሠረት በማድረግ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፡፡

 

አንቀጽ 8የጥቅም ግጭትን ማስወገድ

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

8.1 ለግብይት ሥርዓቱ እና ለደንበኞች ጥቅም ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡

8.2 በደንበኛውና በርሱ መካከል የሚያጋጥመውን የሚታወቅ የጥቅም ግጭት ወዲያውኑ ለምርት ገበያው በፁሁፍ መግለጽ አለበት፡፡ የምርት ገበያውም የጥቅም ግጭቱ በተገለፀለት በአምስት (5) የሥራ ቀናት ውስጥ ይህንኑ ለባለሥልጣኑ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡

አንቀጽ 9ምስጢር መጠበቅ

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

9.1 በሥራ ላይ እያለም ሆነ ሥራውን ከለቀቀ በኋላ በሥራ አጋጣሚ ያወቃቸውን ምስጢራዊ መረጃዎች የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡

9.2 በሥራው ምክንያት ያወቃቸውንና ይፋ እንዳይወጡ በሕግ የተከለከሉ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ወይም ገና በሂደት ላይ የሚገኙ ውሳኔ ያላረፈባቸውን ጉዳዮች ለግል ጥቅም መጠቀም ወይም ለግብይት ተሳታፊዎች በመግለፅ የውስጥ አዋቂ ንግድ እንዲፈጽሙ ወይም ሌላ ተገቢ ያልሆነ ውድድር እንዲያካሂዱ ለማድረግ የሚያስችል ክፍተት መፍጠር የለበትም፡፡

 • ሥልጣን ባለው አካል ካልታዘዘ ወይም ጉዳዩን ማወቅ ለሚገባው አግባብ ላለው አካል ካልሆነ በስተቀር በክትትል ወይም በማጣራት ሂደት ላይ ያለ ጉዳይን አስመልክቶ የማጣራት ሂደቱን ወይም ሊወሰድ የሚገባውን አስተዳደራዊ እርምጃ ሊያሰናክል የሚችል መግለጫ ወይም ለኅዝብ ክፍት ያልሆኑመረጃዎችን ለሦስተኛ ወገን መስጠት የለበትም፡፡
 • በሥራው ምክንያት ጉዳዩን ማወቅ ለሚገባው ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ጠቋሚዎችንና መረጃ ሰጪዎችን ስምና ማንነት መግለፅ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

 አንቀጽ 10ሕግን ማክበር

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

10.1 የሕግ የበላይነትን በማክበር ሥራውን ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ ማከናወን አለበት፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅን፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅን፣ የምርት ገበያውን የውስጥ ደንብ፣ ባለሥልጣኑ በየጊዜው የሚያወጣቸውን መመሪያዎች፣ ትዕዛዞች እና ሌሎች ለሥራው አፈጻጸም ተገቢነት ያላቸውን የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ሕጎች አክብሮ መስራት አለበት፡፡

10.2 የምርት ገበያው የሥራ አመራር እና የሥራ መሪዎች በሕጋዊ ሥልጣናቸው የሚያስተላልፉትን ውሳኔ እና ትዕዛዝ የማክበርና የመፈጸም ኃላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም ሕግን የሚጥስ ውሳኔ እና ትዕዛዝ መፈጸም የለበትም፡፡

10.3 የምርት ገበያው የሥራ አመራር ወይም የሥራ መሪዎች ሕግን የሚጥስ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ማስተላለፍ የለባቸውም፡፡ በሕግ የተቀመጠን ድንጋጌ የሚጥስ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ የተላለፈለት ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ጉዳዩን ለቅርብ ኃላፊው በፅሁፍ ማቅረብ አለበት፡፡ ከቅርብ ኃላፊው ጋር ጉዳዩን በአምስት (5) የሥራ ቀናት ውስጥ መፍታት ካልተቻለ ቅሬታውን ለምርት ገበያው የበላይ ኃላፊ በጽሁፍ ማቅረብ አለበት፡፡ የምርት ገበያው የበላይ ኃላፊ በሚሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወይም ቅሬታውን አቅርቦ በአምስት (5) የሥራቀናት ውስጥ ምላሽ ሳያገኝ የቀረ ሠራተኛ ወይም የሥራ ሃላፊ ጉዳዩን በጽሁፍ ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ማቅረብ አለበት፡፡

 አንቀጽ11  ሕጋዊ በሆነ ሥልጣን መገልገል

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

11.1 ኅብረተሰቡን በአግባቡ እንዲያገለግልና ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በሕግ ተወስኖ በተሰጠው የሥልጣን ገደብ ውስጥ መጠቀም አለበት፡፡ በሥልጣኑ ያለአግባብ መገልገል ወይም ሥልጣኑን ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው የግል ጥቅም ማግኛ ማዋል የለበትም፡፡

11.2 ሥልጣኑን በመጠቀም በሥሩ የሚሠራ ሠራተኛን ወይም የሥራ ኃላፊን ከሕግና ከመመሪያ ውጭ እንዲሰራ ማዘዝና መገፋፋት የለበትም፡፡

11.3 ለሥራ ባልደረባው ወይም ለደንበኞች አማላጅ ሆኖ ጉዳይ ማስፈፀም የለበትም፡፡

 

አንቀጽ 12   ግልፅነት

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

12.1 በአሠራሩ ግልፅ መሆን አለበት፡፡ የግብይት ተሳታፊዎች ሊያውቁት የሚገባን አንድ መረጃ  ለማንኛውም ሦስተኛ ወገን እንዳይገለፅ ካልተከለከለ በስተቀር መረጃ መደበቅ የለበትም፡፡

 • የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች እና አገልግሎቶች በሚመለከት ከደንበኞች ጥያቄ ሲቀርብለት መረጃው ለሦስተኛ ወገን እንዳይገለፅ የተከለከለ ካልሆነ በስተቀር ሕግና መመሪያን ተከትሎ ተገቢውን ማብራሪያ ወይም ምላሽ መስጠት አለበት፡፡
 • ለሚሰጠው አገልግሎት በሕግ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎችና ለሚሰጠውም ውሳኔ ምክንያት መግለፅ አለበት፡፡

12.4 የአገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ ከደንበኞች ለሚቀርብለት ጥያቄ ወቅታዊና ተገቢ ማብራሪያ፣ ምላሽና መረጃ መስጠት አለበት፡፡

12.5 አግባብነት ባለው የምርት ገበያው የውስጥ ደንብ እና የአሠራር ማንዋል መሠረት መደራጀት ያለበትን መዝገብ ወይም ሰነድ በተገቢው መንገድ ማደራጀት፣ መመዝገብ ያለበትን መረጃ በትክክል እና በወቅቱ መመዝገብ ወይም መሰጠት ያለበትን ማስታወቂያ/ማስጠንቀቂያ በወቅቱ መስጠት አለበት፡፡

12.6 ሥልጣን ሳይኖረው መረጃዎችን እና ሰነዶችን መፍጠር/ማዘጋጀት፣ ማየት፣ መለወጥ፣

መሰረዝ፣ ማጥፋት ወይም ላልተፈቀደለት ዓላማ ማዋል የለበትም፡፡

 አንቀጽ 13 ለደንበኞች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት፡

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

13.1 የሕዝብ አገልጋይነትን ስሜትና ባሕርይ ተላብሶ ሥራውን ማከናወን አለበት፡፡

13.2 ለደንበኞች ተገቢውን አክብሮት በመስጠትና ትህትና በማሳየት ለሚቀርብለት ጥያቄ በተቀመጠው የአገልግሎት አሰጣጥ የጥራት ደረጃና የጊዜ ገደብ ስታንዳርድ መሠረት ምላሽ መስጠት አለበት፡፡

13.3 ለደንበኞች ስለሚያከናውነው ሥራ እና ስለሚከተለው የአሠራር ሥርዓት ያልተዛባና ትክክለኛ መረጃ መስጠት አለበት፡፡

 

አንቀፅ 14 ስጦታ እና መስተንግዶ አለመቀበል፡

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን ለሚሰጠው አገልግሎት ሥራውን ከማከናወኑ በፊትም ሆነ ሥራውን ካከናወነ በኋላ ከደንበኞች ለራሱ፣ ለቤተሰብ አባል ወይም ለቅርብ ዘመዱ ማንኛውንም ስጦታ፣ ክፍያ ወይም መስተንግዶ መቀበል የለበትም፡፡

 

አንቀጽ 15 ከማጭበርበር እና ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን የግብይት ተሳታፊዎችን ከማጭበርበር፣ ከማታለል፣ ትክክለኛ ያልሆኑ እና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ መረጃዎችን ከማሰራጨት ድርጊት መቆጠብ አለበት፡፡

 አንቀጽ16በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንደ ግብይት ተሳታፊ አለመሳተፍ፡

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

16.1 ከግብይት ተሳታፊዎች ጋር የግል የሥራ ግንኙነት ሊኖረው አይገባም፡፡

16.2 በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በቀጥታ በግሉ፣ የሽርክና ማኅበር አባል፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለአክሲዮን ወይም የኅብረት ሥራ ማኅበር አባል በመሆን በባለሥልጣኑ ዕውቅና የተሰጠው የምርት ገበያ አባል፣ አባል ያልሆነ ቀጥታ ተገበያይ፣ የመድረክ-የግብይት ወኪል፣ የመጋዘን ወኪል፣ የአገናኝ አባል ደንበኛ፣ የመጋዘን አገልግሎት ሰጪ፣ የኢንቨስትመንት አማካሪ፣ የሕግ አማካሪ፣ የሂሣብ አዋቂ ወይም ገለልተኛ ኦዲተር ሆኖ መሳተፍ አይችልም፡፡

16.3 በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተው ቢኖርም በሌላ ሕግ በግልፅ ካልተከለከለበ ስተቀር በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከቱት ድርጅቶች የአክሲዮን ማኅበር ከሆኑ ባለአክሲዮን ከመሆን ወይም በማንኛውም አይነት የንግድ ድርጅት ያለውን የአክሲዮን ድርሻ በአገናኝ አባል በኩል ከመሸጥ አይከለክለውም፡፡ ሆኖም በማንኛውም የንግድ ድርጅት ያለውን የአክሲዮን ድርሻ በአገናኝ አባል በኩል ለመሸጥ ሲዋዋል ወይም ባለአክሲዮን የሆነበት የአክሲዮን ማኅበር በባለሥልጣኑ እውቅና የተሰጠው የምርት ገበያው አባል፣ አባል ያልሆነ ቀጥታ ተገበያይ፣ የመድረክ/የግብይትወኪል፣ የመጋዘን ወኪል፣ የክፍያ መፈጸሚያ ተቋም፣ የመጋዘን አገልግሎት ሰጪ፣ የኢንቨስትመንት አማካሪ፣ የሕግ አማካሪ፣ የሂሣብ አዋቂ ወይም ገለልተኛ ኦዲተር መሆኑን ካወቀ ወይም ማወቅ ነበረበት የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ካለ ይህንኑ ለምርት ገበያው በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የምርት ገበያውም ይኸው በተገለፀለት በአምስት (5) የሥራ ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡

16.4 በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በቀጥታ በግሉ፣ የሽርክና ማኅበር አባል፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለአክሲዮን ወይም የኅብረት ሥራ ማኅበር አባል የሆነ በባለሥልጣኑ ዕውቅና የተሰጠው የምርት ገበያአባል፣ አባል ያልሆነ ቀጥታ ተገበያይ፣ የመድረክ/የግብይት ወኪል፣ የመጋዘን ወኪል፣ የመጋዘን አገልግሎት ሰጪ፣ የኢንቨስትመንት አማካሪ፣ የሕግአማካሪ፣ የሂሣብ አዋቂ ወይም ገለልተኛ ኦዲተር ወይም የምርት ገበያው ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ የሆነ ቤተሰብ ወይም የቅርብ ዘመድ ያለው መሆኑን ካወቀ ወይም ማወቅ ነበረበት የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ካለ ይህንኑ ለምርት ገበያው በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የምርት ገበያውም ይኸው በተገለፀለት በአምስት (5) የሥራ ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ በሌላ ሕግ በግልፅ ካልተከለከለ በስተቀር ከዚህ በላይ የተመለከተው የማሳወቅ ግዴታ ግልፅነትን በመፍጠር ተገቢውን ክትትል ለማድረግ እንጂ በምርት ገበያው ተቀጥሮ ከመሥራት አይከለክልም፡፡

አንቀጽ 17ስለግብይት ተሳታፊዎች ድጋፍ እና ክትትል

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ በግብይት ተሳታፊዎች ላይ የድጋፍ፣ የክትትል እና የምርመራ ሥራውን ሲያከናውን በቸልተኝነትም ሆነ ሆንብሎ ድጋፍ ለሚያስፈልገው ተገቢውን ድጋፍ አለማድረግ፣ የግብይት ተሳታፊዎች እንዲተገብሯቸው በሕግ የተደነገጉ ግዴታዎችን በአግባቡ እየተገበሩ እንዳልሆነ በክትትል ወቅት ደርሶበት ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ ወይም ለሚመለከተው ክፍል እርምጃ እንዲወሰድ ሪፖርት አለማቅረብ እንዲሁም ያልተፈጠሩ ክፍተቶችን እንደተፈጠሩ አድርጎ ሀሰተኛ ሪፖርት ማቅረብ የተከለከለ ነው፡፡

 አንቀጽ 18፡- ስለ ምርት ማከማቻ መጋዘን እና ማእከላዊ ማከማቻ አሠራር

እያንዳንዱ ሠራተኛ እና የሥራ ኀላፊ ሥራውን ሲያከናውን እንደ የሥራ ድርሻው፡

18.1 ትክክለኛ የናሙና መውሰጃ፣ የደረጃ መወሰኛ ወይም የክብደት መለኪያ መሣሪያ       

     በመጠቀም ሥራውን በትክክል ማከናወን አለበት፡፡

18.2 በምርት ገበያው የውስጥ ደንብ እና አግባብነት ባለው የአሠራር ማንዋል የተቀመጡትን የምርት ናሙና አወሳሰድ፣ የሚስጢር መለያ/ኮድ አሰጣጥ፣ የደረጃ አሰጣጥ፣ የክብደት አለካክ፣ የምርት ርክክብ ወይም የምርት ክምችት አያያዝ የአሠራር ሂደቶችን በጥብቅ መከተል አለበት፡፡

18.3 ትክክለኛ እና ወካይ ናሙና መውሰድ አለበት፡፡

18.4 የርጥበት ደረጃውን ያልጠበቀ፣ የተበላሸ ወይም የተቀላቀለ ምርት እንዲያልፍ ማድረግ

የለበትም፡፡

18.5 ለተወሰደ የምርት ናሙና የተሳሳተ የሚስጢር መለያ/ኮድ መስጠት ወይም የተለያዩ

የምርት ናሙናዎችን የሚስጢር መለያ/ኮድ ማለዋወጥ የለበትም፡፡

18.6 የምርቱን ደረጃ በተሳሳተ መንገድ ማውጣት እና ለምርቱ የተዛባ ደረጃ መስጠት ወይም

የተለያዩ የምርት ናሙናዎችን ደረጃ ማለዋወጥ የለበትም፡፡

18.7 የምርቱን ክብደት በተሳሳተ መንገድ መለካትና ውጤቱ የተዛባ እንዲሆን ማድረግ

የለበትም፡፡

18.8 የምርት ርክክብ የኤሌክትሮኒክስ ማስታወሻ፣ የማከማቻ መጋዘን ኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ፣ የማንሻ ማስታወሻ እና የምርት መረከቢያ ማስታወሻ የመሳሰሉትን ሰነዶች ያለአግባብ መፍጠር፣ መለወጥ፣ መሰረዝ፣ ማጥፋት ወይም የመለያቁጥሮችን ማዛባት የለበትም፡፡

18.9 የደንበኞች ምርት በማከማቻ መጋዘን በሚቆይበት ጊዜ ጥራቱ እንዲጓደልበምርት ገበያው በሥራ ላይ ካለው የእርጥበት ማካካሻ መጠን በላይ መጠኑ እንዲቀንስ ወይም ምርቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲጠፋ ማድረግ የለበትም፡፡

አንቀጽ 19–  ተጠያቂነት

ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን ሲያከናውን፡-

 • ለሚሠራው ሥራ፣ ለሚወስነው ውሳኔና ለሚወስደው እርምጃ ኃላፊ

ነው፡፡

 • ሥራውን በአግባቡ ስለማከናወኑና ኃላፊነቱን በትክክል ስለመወጣቱ በሕግ

መብት ከተሰጠው አካል ተገቢው ጥያቄ ሲቀርብለት አስፈላጊውን

ማብራሪያ እና ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

 • የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ከሆነ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እና

የአሠራር ግድፈት ሲኖር በወቅቱ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

 • ያከናወናቸውን ሥራዎች በተመለከተ ለሚመለከተው የሥራ ኃላፊ እና

የሥራ ክፍል ወቅታዊ ሪፖርት ማቅረብ አለበት፡፡

 • የሚያቀርበው ሪፖርት በእውነተኛና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ

መሆን አለበት፡፡

ክፍል ሦስት

ስለ ሕግ ጥሰቶች እና ቅጣቶች

 አንቀጽ 20፡- የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት ዓይነቶች፡-

20.1 የጥፋቶችን ክብደት ግምት ውስጥ በማስገባት ለዚህ መመሪያ አፈጻጸም የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት ዓይነቶች ከከባድ ወደ ቀላል ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ተመድበዋል፡፡

20.2 አንደኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰቶች የሚባሉት የመመሪያውን አንቀጽ 5.1፣ 5.3፣ 9.2፣ 9.4፣ 11.1፣ 12.6፣ 14፣ 15፣ 16.1፣ 16.2፣ 18.4፣ 18.8 እና 18.9 በመተላለፍ የሚፈጸሙ ጥፋቶች ናቸው፡፡

20.3 ሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰቶች የሚባሉት የመመሪያውን አንቀጽ 5.2፣ 6.2፣ 7፣ 8.1፣ 9.3፣ 10.2፣ 11.2፣ 12.5፣ 16.3፣ 17፣ 18.1፣ 18.2፣ 18.3፣ 18.5፣ 18.6፣ 18.7፣ 19.3 እና 19.5 በመተላለፍ የሚፈጸሙ ጥፋቶች ናቸው፡፡

20.4 ሦስተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰቶች የሚባሉት የመመሪያውን አንቀጽ 6.1፣ 6.3፣ 6.4፣ 6.5፣ 8.2፣ 9.1፣ 10.1፣ 11.3፣ 12.1፣ 12.2፣ 12.3፣ 12.4፣ 13.1፣ 13.2፣ 13.3፣ 16.4፣ 19.2 እና 19.4 በመተላለፍ የሚፈጸሙ ጥፋቶች ናቸው፡፡፡

20.5 ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ በሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ ከተቀጣ በኋላ በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ ጥፋተኛ ሆኖ የተቀጣበትን ወይም ሌላ የሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት በመፈፀም አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የቀድሞው የጥፋት ሪከርድ እንደ ማክበጃ ተይዞ በአንደኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት ቅጣት ይቀጣል፡፡

20.6 ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ በሦስተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ ከተቀጣ በኋላ በሦስት አመታት ጊዜ ውስጥ ጥፋተኛ ሆኖ የተቀጣበትን ወይም ሌላ የሦስተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት በመፈፀም አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የቀድሞው የጥፋት ሪከርድ እንደ ማክበጃ ተይዞ በሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት ቅጣት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ21፡- ስለ ቅጣት

21.1 ባለሥልጣኑ አግባብነት ካላቸው የሥራ ክፍሎች ወይም ከሌላ ማንኛውም ሰው በሚቀርብለት ጥቆማ ወይም በራሱ ተነሳሽነት በማንኛውም የምርት ገበያው ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ላይ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ምርመራ ካደረገ በኋላ አስተዳደራዊ ክስ አቅርቦ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 20 የተመለከቱትን ጥፋቶች መፈጸሙን ሲያረጋግጥ በዚህ አንቀጽ የተመለከቱትን አስተዳደራዊ እርምጃዎች መውሰድ ይችላል፡፡

21.2 የአንደኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት በመፈፀም ወይም በሁለት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት በመፈፀም አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ እንደ ጥፋቱ ክብደት ከሥራ ደረጃ እና ከደመወዝ ዝቅ በማድረግ ወይም ከሥራ በማሰናበት ይቀጣል፡፡

21.3 የሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት በመፈፀም ወይም በሦስት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የሦስተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት በመፈፀም አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ እንደ ጥፋቱ ክብደት እስከ ሦስት ወር ደሞዝ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

21.4 በሦስተኛ ደረጃ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት አስተዳደራዊ ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ

ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሠራተኛ ወይም የስራ ኃላፊ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይቀጣል፡፡

21.5 በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (21.2)፣ (21.3) እና (21.4) የተመለከቱት ቅጣቶች እንደተጠበቁ ሆነው የጥፋተኝነት ውሳኔ እና ቅጣት የተላለፈበት ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ለባለሥልጣኑ ቦርድ ይግባኝ ሳያቀርብ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 22 የተመለከተው የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜ ካለፈ ወይም ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ለሌሎች አስተማሪ እንዲሆን ባለሥልጣኑ የሠራተኛውን ወይም የሥራ ኃላፊውን ስም፣ የሥራ ደረጃ፣ የሥራ መደብ መጠሪያ፣ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘበትን የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት እና የተጣለበትን ቅጣት የሚገልፅ የፅሁፍ ማስታወቂያ በምርት ገበያው፣ በብሄራ ዊግብይት ፈጻሚዎች ማህበር እና በባለሥልጣኑ የማስታወቂያ መለጠፊያ ሰሌዳዎች እንዲሁም በባለሥልጣኑ ድረገጽ ላይ ለሰላሳ (30) ተከታታይ ቀናት ተለጥፎ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡

21.6 የጥፋተኝነት ውሳኔ እና ቅጣት የተላለፈበት ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ለባለሥልጣኑ ቦርድ ይግባኝ ሳያቀርብ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 22 የተመለከተው የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜ ካለፈ ወይም ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ባለሥልጣኑ በዚህ አንቀጽ መሠረት በሠራተኛው ወይም በሥራ ኃላፊው ላይ ያስተላለፈውን የውሳኔ ግልባጭ ለምርት ገበያው በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡

21.7 የምርት ገበያው በሠራተኛው ወይም በሥራ ኃላፊው ላይ የተወሰነው የጥፋተኝነት ውሳኔ እና ቅጣት በደረሰው ከሰላሳ (30) ተከታታይ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (21.2) እና (21.3) መሠረት የተወሰነውን ቅጣት በማስፈጸም ውጤቱን ለባለሥልጣኑ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡

21.8 የምርት ገበያው ውሳኔው በደረሰው ከሰላሳ (30) ተከታታይ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በሠራተኛው0 ወይም በሥራ ኃላፊው ላይ የተወሰነውን ቅጣት በማስፈጸም ውጤቱን በጽሁፍ ለባለሥልጣኑ ካላሳወቀ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (21.2) ለተመለከተው ቅጣት በብር ሀምሳ ሺህ (50,000) እንዲሁም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (21.3) ለተመለከተው ቅጣት በብር ሰላሳ ሺህ (30,000) የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለስልጣኑ የምርት ገበያው ያላስፈፀማቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በፅሁፍ ሪፖርት ያደርጋል፡፡

21.9 ባለልጣኑ የተፈጸመው የሥነ-ምግባር ሕጥሰት ወንጀል ሆኖ ሲያገኘው በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 551/1999 አንቀጽ 7 (2) በተደነገገው መሠረት በሕግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት በኩል ጉዳዩን ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ማስተላለፍ እና መከታተል አለበት፡፡

 አንቀጽ 22ስለ ይግባኝ

በዚህ መመሪያ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ (21.2)፣ (21.3) እና (21.4)  መሠረት ባለሥልጣኑ ባስተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ እና/ወይም በተጣለው ቅጣት ቅሬታ ያለው ተከራካሪ ወገን ውሳኔው በተሰጠ በአስራ አምስት (15) ተከታታይ ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ ቦርድ ይግባኝ ማቅረብ ይችላል፡፡

 ክፍል አራት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

 አንቀጽ 23ስለ ይርጋ

በዚህ መመርያ መሠረት በማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ላይ የሚቀርብ አስተዳደራዊ ክስ ድርጊቱ መፈጸሙ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ ከ 2 ዓመት በኋላ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ ከ5 ዓመት በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡

 አንቀጽ 24፡-የባለልጣኑ ኃላፊነት

ባለሥልጣኑ፤

24.1 መመሪያውን በድረገጹ እና በወረቀት አትሞ ለምርት ገበያው ሠራተኞች እና ለባለድርሻ አካላት ያሰራጫል፡፡

24.2 ስለ መመርያው ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ለብኄራዊ ግብይት ፈጻሚዎች ማህበር እና ለባለሥልጣኑ ሠራተኞች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ለግብይት ተሳታፊዎች እና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል፡

24.3 የባለሥልጣኑ የሕግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ማንኛውም ሠራተኛ ወይም የሥራ ኃላፊ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ የሥነ-ምግባር ሕግ ጥሰት ስለመፈጸሙ አግባብነት ካላቸው የባለሥልጣኑ የሥራ ክፍሎች ወይም ከሌላ ማንኛውም ሰው ጥቆማ ሲቀርብለት ወይም በራሱ ተነሳሽነት/አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ምርመራ በማድረግ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ አስተዳደራዊ ክስ በመመስረት ጉዳዩን ይከታተላል፤ ጉዳዩ ውሳኔ ካገኘ በኋላም አፈጻጸሙን ይከታተላል፡፡፡፡

 አንቀጽ 25–  ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ሕጎች

የዚህን መመርያ ድንጋጌዎች የሚቃረን ማንኛውም መመርያ፣ የውስጥ ደንብ ወይም ልማዳዊ አሠራር በዚህ መመርያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

አንቀጽ 26፡-መመርያው ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን

በቂ የመሰናዶ ጊዜ ለመስጠት ሲባል መመሪያው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለልጣን ቦርድ ከፀደቀ ከሦስት ወራት በኋላ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ቦርድ

 ጥቅምት 6 ቀን 2013..   ፀደቀ